PHOTO GALLERY

KICKOFF CONFERENCE


ከሁሉም  በላይ የሆነውን የአንዱን አምላክ መኖር ለዓለም ያስተዋወቁ እሥራዔላውያን መሆናቸው ይታወቃል። የሕይወት ቃል የሆነውንም መጽሐፍ ቅዱስን ያገኘነው በእነርሱ አማካይነት ነው። ስለዚህም በተለይ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የእሥራዔላውያንን ታሪክ፤ የተለያዩ ልማዳቸውንና ባሕላቸውንም ጭምር ተጽፎ እናገኛለን። እሥራኤላውያን እግዚአብሔር ፈቃዱንና ሃሳቡን የገለጸባቸው ሕዝብ ቢሆኑም ብዙ የፈጸሙት ስህተትና አጉል ባህልም ነበራቸውና ይህም ለትምህርታችን እንዲሆን በዚሁ ክፍል ውስጥ ተጽፏል። ለምሳሌ ማቴ. 19፤8-9 እንደምናየው ጌታ፤ " አስቀድሞ እንዲህ አልነበረም ግን፤ ....." እያለ የተናገረበት ክፍል አለ። ይህም እስራኤላውያን ይለማመዱት የነበረው ነገር ሁሉ ትክክል ነበር ማለት እንዳልሆነ ያሳየናል።

 

ድሮ በእሥራኤል አገር ባህል  ሴት እንደንብረት ነበር የምትቆጠረው። በብዙ ጉዳዮች ላይ የራሷ የሆነ ውሳኔ አልነበራትም። ለትዳርም እንኳን የሚሰጧት ወላጆቿ ነበሩ። ሴት የንብረት ባለቤትነት መብት / Property Right /  አልነበራትም። ወንድ ልጅ የሌላት በሚሆንበት ጊዜ ብቻ አንዳንድ ጊዜ ይህ መብት ይሰጣት ነበር። የሴት ቃለ መሐላ / Vow / በቀላሉ በባሏ ወይም በአባቷ ሊፈርስ ይችል ነበር፤ የወንዱ ግን የጸና ነበር።

 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ  ታሪክን እስከለወጠበት ጊዜ ድረስ ሴት እንደ ወንድ የእግዚአብሔርን ቃል መድገም / recite / ማድረግ አትችልም ነበር። በጉባዔ መካከል አትፀልይም ነበር፤ በአምልኮም ቦታ በአገልግሎት ተሳትፎ አልነበራትም፤ ሴቶች የሚቀመጡትም እንኳ ለብቻቸው ነበር።

 

ይህ በጣም ያስገርመን ይሆናል። ነገር ግን በዚያን ዘመን ግሪኮች፤ ሌሎችም ወገኖች፤ ዛሬም እንኳን እሥራዔላዊ ያልሆኑት የመካከለኛው ምሥራቅ ባሕሎች ለምሳሌ አረቦች ሴቶችን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያዩ ስናይ በብሉይ የምናገኘው የአይሁድ ባሕል የተሻለ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ባሕሎች የበለጠ ለሴት ቦታ ሲሰጥ እናያለን።

 

ብዙ ሳንሄድ በብሉይ ዘመን የኖሩ ነበሩ ብዙዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የታወቁት የእምነት እናቶች። በዚያ ባህል  ውስጥ እነርሱን የመሰለ ብዙ ጥበብ የሞላባቸው፣ ባሎቻቸውን እና ሕዝባቸውን በጠቅላላ መሳብ / Influence / ማድረግ የቻሉ ሴቶች ማፍራት ተችሏል። ሣራን የመሰለ የእምነት እናት፣ አሥቴርን የመሰለ ታሪክን የለወጠች ልዕልት፣ዲቦራን የመሰለች ነቢይትና መሪ፣.......ልሎችም ተቆጥረው የማያልቁ የታሪክ ሴቶች አሉ።

 

ከላይ እንደጠቀስነው ክርስቶስ ታሪክን ለውጧል ብለናል። የሰዎችን ሕይወት ሁሉ ነክቷል። በቃል ሳይሆን በሕይወቱ ብዙ ዘመን  የቆዩትን ባሕሎች፣ ልማዶች ነቅንቋል። ፍቅሩም ወሰን የለውም  ነበር። ሰዎች የማይቀርቧቸውን፣ በዚያን ዘመን እንደርኩስ የሚቆጠሩትን ለምጻሞችና በሽተኞች ሳይቀር ዳስሷል።

 

ጌታ በመምጣቱ ከዚህ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች  ሽሮ ከዚህ በፊት ያልነበረን አዲስ ሕብረተሰብን ከአሕዛብ ይሁን ከአይሁድ የተውጣጡትን መሰረተ። ይህችም አዲስ ተቋም ቤተክርስቲያን ስትሆን፣ በቤተክርስቲያን " ነፃነት " ፣ " እኩልነት " መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። ክርስትና ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ትልቅ ክብርና ቦታ ከወንዶች እኩል አላቸው። ጌታ የመሠረታት ቅድስት ቤተክርስቲያን እንኳን በሴት ትመሰላለች።

 

ሴቶች በመፅሐፍ  ቅዱስ ውስጥ እንደምናየው ከመስቀሉ አጠገብ ለመለየት የመጨረሻው ናቸው። ጌታ ኢየሱስ በጭንቅ  በነበረበት ጊዜ ተከታዮቹ ሁሉ ሸሽተውት ነበር፣ ደቀመዛሙርቱም አልቆዩም። ሴቶች ግን ጌታ መስቀል ሥር እስከመጨረሻው ቆይተው ፍቅራቸውን ገልጸዋል።

 

ጌታ ከተቀበረም በኃላ ደቀመዛሙርቱ / ወንዶች / በር ዘግተው ፈርተው ተቀምጠው ሳለ ሴት ነች ከሁሉ ቀድማ ያንን ፍቅር፣ ያንን ጌታ አስከሬኑን ለማየት በመጀመሪያ ወደመቃብሩ የሄደች። ክርስቶስም ከሞት ከተነሣ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው ሴት ነች። የትንሣኤውንም አዋጅ፣ የመጀመሪያውን  የወንጌል አዋጅ  ለማወጅ የተላከችና " ጌታ ተነስቷል " እያለች ያወጀች ሴት ነች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በስሙ ያመኑ ሴቶች የወንጌሉ መልእክተኞች፣ የመስቀሉ አርበኞች ፣ የከርስቶስ ወዳጆች በመሆን በክርስትና ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

 

ክርስትና በመሠረቱ ሴት ክብሯን የተቀዳጀችበት መሠረታዊ የነጻነት ሰነዷ ነው። በአረመኔነት /Heathenism/  የሚታወቁት ከአይሁድ ውጭ የነበሩት ሕዝቦች ባሕሎች ለሴት  አንድም ነፃነት አይሰጡም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት /Judaism/  እንኳን ለሴት የሰጣት ነጻነት አለ ከነዚህ ጋር ሲወዳደር። ዳሩ ግን በጣም ጥቂት ነበር። ክርስትና ግን በአንዲት ቃል ፍጹም ነፃነቷን እንዲህ ሲል ያውጅላታል።

 

                 " በክርስቶስ ኢየሱስ ወንድ የለም ፣ ሴትም የለም። " ገላ 3፣28

 

ስለዚህ አንዳንዶች እንደሚገምቱት ክርስትና ሴትን የሚያሳንስ እምነት አይደለም።

 

ጌታ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ካፈረሳቸው የልዩነት  ግድግዳዎች መካከል ሶስቱ በጣም የታወቁ ናቸው፤ በገላ፤ 3፣28 እና በሌላም ቦታ እንደተገለጸው፣

 

1ኛ       አይሁዳዊ ወይንም ግሪክ / አህዛብ / የሚል  ልዩነት የለም። ድሮ ነበር። ጌታ ግን ሲመጣ

           ሁለቱን አንድ አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ፤ እኩል መሆን ተቻለ።

2ኛ      "ባሪያ የለም ፣ ጨዋ የለም። " በክርስቶስ እገሌ ሃብታም ነው፣ እገሌ ደሃ ነው የሚል  ልዩነት

          የለም።  ሰዎችን በኑሮ ደረጃና መደብ መከፋፈል የለም።

3ኛ       በሴቶች እና በወንዶች መካከል የነበረው ልዩነትም ፈረሰ።

 

ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳረገ ደቀመዛሙርቱ ሲሰበሰቡ  የሐዋሪያት ሥራ. 1፣12-14 ላይ ሴቶችም በዚያ እንደነበሩ የምናየው። ሴቶችና ወንዶች  እኩል በአንድ ላይ አብረው ሲያመልኩ፣ አብረው ሲማሩ፣ አብረው ሲያገለግሉ እናያለን። ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሣ ቀን ስብከቱ በጠቀሰው የብሉይ ጥቅስ ላይ እንኳን ያለው፣ " .......ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ትሆናላችሁ።" ነው። በአይሁዶች እና በአሕዛብ ያልታየ መብትና እኩልነት በክርስትና ውስጥ ተገኘ።

 

በሐዋሪያት ሥራ እንደምናነበው አቄላና ጵርስቅላ የሚባሉት ባልና ሚስት እኩል ጌታን ሲያገለግሉና ለጳውሎስ ብዙ መጽናናት ሲሆኑ እናያለን። የሐዋሪያት ሥራ 9፣36-37  ደግሞ በኢዮጴ ጣቢታ ወይም ዶርቃ የምትባል በመልካም ተግባርና አገልግሎቷ የታወቀች "ደቀመዝሙር" እንደነበረች ይናገራል።

 

የድሮ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በየሰው ቤት ነበር የተመሰረቱት ፤ ታዲያ በዚህ ውስጥ ሴቶች ብዙ ተሳትፎ እንደነበራቸው ግልፅ ነው። ይህ ሁሉ ለውጥ የተገኘው በክርስቶስ ነው።

 

ጌታ ኢየሱስ አገልግሎቱን እንዲያካሂድ በገንዘብ የረዱት ሴቶች ናቸው። ሉቃስ 8፣2-3

 

በኢየሱስ እና በሴቶች መካከል ስለነበረው የቅርብ ጓደኝነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑትን በተለይ በቢታኒያ ይኖሩ የነበሩት የአልአዛር እህቶች ማርታና ማርያም ናቸው። ዮሐንስ 11፣5 ላይ ደስ የሚል ቃል አለ። " ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን ወንድማቸውንም አልዓዛር ይወድ ነበር " ይላል።

 

ወንድማቸው በሞተ ጊዜ ማርታ በተናገረችው ቃል በጌታ ትንሣዔና ሕይወትነት ያላትን እምነት በመናገር ታላቅነቷን አረጋግጣለች። / ዮሐንስ 11፣24-27 /

 

በሌላም ቦታ ሴቶች ጌታን ሽቶ ሳይቀር እየቀቡ እንዳከበሩትና እንደቀረቡት እናያለን።

 

ሰማሪያ ውስጥ ጌታ ያደረገውን ደግሞ በዮሐንስ ወንጌል 4፣7-30 ስናይ በጣም እንገረማለን። ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ቁጭ ብሎ ሲነጋገር ድርብርብ አጥር ነበር ያፈረሰው።

 

 

 

1ኛ    አይሁዳዊት አልነበረችም፣ በዚያን ጊዜ ይህ ትልቅ ነገር ነበር፣ አይሁዳውያን እና ሳምራውያን ብዙ
        ልዩነት ነበራቸው። እርሷም  ራሷ እንኳን በዚህ ተደንቃለች።

2ኛ    ሴት ነበረች፤ ደቀመዛሙርቱ ከሄዱበት ሲመለሱ፣ " ከሴት ጋር ሲነጋገር በማየታቸው ተገረሙ። "

        የሚል ቃል ዮሐንስ 4፣27 ላይ እናገኛለን።

 

ጌታ ሴቶችንም እንደወንዶች እኩል ፈውሷል፣ ይህ የሚያሳየው ፍቅሩና ርህራሄው እኩል እንደሆነ

 ነው። / ማርቆስ 1፣29-30 ላይ የጴጥሮስን አማት ፈውሷል። ማርቆስ 5፣21-43 የዳርዮስን ሴት ልጅ  አድኗል። /

 

ጾታና ዘር ሳይመርጥ አሕዛቧን  ሴት እንኳን ፈውሷል። / ማርቆስ 7፣24-30 በጌታ ዘንድ

"ሁለተኛ ጾታ"  የሚባል ነገር የለም። /

 

ከመጀመሪያይቱ ሴት ከሔዋን ጀምሮ ሴቶች ምንም የጎደላቸው አይደሉም። እንዳውም ሔዋን ማለት " የሕያዋን እናት " ወይም " ሕይወት ያላቸው ሁሉ እናት " ነው። የእባቡን እራስ ይቀጠቅጣል የተባለው ጌታ ኢየሱስ እንኳን " የሴቲቱ ዘር " ተብሎ ነው የተጠራው።

 

እግዚአብሔር ሴትንም ሆነ ወንድን ሁለቱንም መለኮታዊ እጁ ስለፈጠራቸው ለእርሱ ሁለቱም እኩል ናቸው። እነሆ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነው። ሁለቱም በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አላቸው።

 

 

ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ

በውሂብ ዘውዴ የቀረበ

Navigate

Contact

Connect

More ways to
connect with us

Our number:

713-484-5530

Our email:

ecfc@ecfchouston.org

Our address:

401 Present St.

Missouri City, TX 77489

© 2005-2022 Ethiopian Christians Fellowship Church. All  Rights Reserved.  |   401 Present St. Missouri City, TX 77489  |   (713) 484-5530  |  ecfc@ecfchouston.org